ቅ. ሥላሴ ካቴድራል

{gallery}pic-cathedral{/gallery}

ቅ. ሥላሴ ካቴድራል

{gallery}pic-cathedral{/gallery}

ቅ. ሥላሴ ካቴድራል

{gallery}pic-cathedral{/gallery}

ቅ. ሥላሴ ካቴድራል

{gallery}pic-cathedral{/gallery}

http://www.trinity.eotc.org.et/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/46016501.jpg http://www.trinity.eotc.org.et/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/7472451.jpg http://www.trinity.eotc.org.et/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/395795church_4.jpg http://www.trinity.eotc.org.et/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/357816church_5.jpg
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ የ2007 ዓ.ም.የልደት በዓልን አስመልከቶ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ

0908

ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በእንተ በዓለ ልደት ዓቢይ ዘእግዚእነ ወአምላክነ  ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ሎቱ ስብሐት ፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ
አሜን!!

-    በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፤
-    ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤
-    የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤
-    በሕመም ምክንያት በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤
-    እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤
የዘለዓለም አባት፣ የሰላም አለቃ፣ ስሙም ድንቅ መካርና ኃያል አምላክ የሆነው ጌታችን፣ አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለሁለት ሺሕ ሰባት ዓመተ ምሕረት በዓለ ልደቱ በሰላም አደረሳችሁ!!
‹‹ወውእቱ ቃል ሥጋ ኮነ ወኃደረ ላዕሌነ፤ ያ ቃል ሥጋ ሆነ፤ በእኛ ላይም አደረ›› (ዮሐ. 1፣14) 

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!
የጌታችን፣ የአምላካችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን በዓለ ልደት ስናከብር ከሁሉ በፊት የእርሱን ማንነት በማውሳት፣ በመረዳትና የእምነት ግብረ መልስን በመስጠት ልናከብር እንደሚገባ መገንዘቡ ተገቢ ነው፤
ከዚህ አኳያ ለመሆኑ የተወለደው ማን ነው? ለምንስ ተወለደ? በልደቱ ዕለት ለዓለም የተላለፈው አጠቃላይ መልእክትስ ምንድን ነው? የሚለውን ማየት በእጅጉ አስፈላጊ ነው፤
ቅዱሳት መጻሕፍት በግልጽ እንደሚያስተምሩን ከሦስቱ አካላተ እግዚአብሔር አንዱ የሆነው እግዚአብሔር ወልድ የአብና የመንፈስ ቅዱስ ቃል ስለሆነ በተለየ ኩነቱ ቃል፣ ቃለ አብ፣ ቃለ እግዚአብሔር፣ አካላዊ ቃል ተብሎ ይጠራል፤ (መዝ. 32፣6፤ ዮሐ. 1፣1-2፤ ራእ. 19፣13)
ቃል ከልብ እንደሚገኝ አካላዊ ቃልም ከአብ የተገኘ ነው፤ ይሁንና ቃል ከልብ በመገኘቱ ደኃራዊ አይባልም፤ ልብም ቃልን በማስገኘቱ ይቀድማል አይባልም፣
በተመሳሳይም አካላዊ ቃል ከአብ በመገኘቱ ደኃራዊ አይባልም፣ የአካላዊ ቃል አስገኝ የሆነው አብም አስገኝ በመሆኑ ከወልድ ይቀድማል አይባልም፡፡
በህልውናም (በአኗኗር) ከቃል የተለየ ወይም የቀደመ ልብ እንደማይኖር ሁሉ፣ ከአካላዊ ቃል የተለየ ወይም የቀደመ የአብ ህልውና (አኗኗር) የለም፤
ቃል የሚለው ስም እኩል የሆኑ የሦስቱ አካላተ እግዚአብሔር ቅድምና እና ህልውና በምሥጢር ያገናዘበና በትክክል የሚገልጽ በመሆኑ ወንጌላዊው ዮሐንስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በመለኮታዊና በቀዳማዊ ስሙ ቃል ብሎታል፤
ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ‹‹በመጀመሪያው ቃል ነበረ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ፤ ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤
ሁሉ በእርሱ ሆነ፣ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም›› በማለት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን እግዚአብሔርነት በማያሻማ መልኩ ያረጋግጣል፤ (ዮሐ. 1፣1-3)፡፡
እግዚአብሔር አብ አካላዊ በሆነ ቃሉ በእግዚአብሔር ወልድ ፍጥረታትን ሁሉ እንደፈጠረ፣ አካላዊ በሆነ እስትንፋሱ በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም ለሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ ሕይወትን እንደሰጠ በቅዱስ መጽሐፍ በብዙ ቦታ በግልጽ ተቀምጦአል፤ (ዘፍ. 1፣1-3፤ መዝ. 32፣6፤ ዘፍ. 2፣7፤ ሮሜ 8፣11)፡፡
በመሆኑም ከጊዜ በኋላ ሥጋችንን በመዋሐድ ሰው ሆኖ ተወለደ እየተባለ ያለው ፍጥረታትን በሙ ሉ የፈጠረ፣ ከተፈጠረው ፍጥረት አንዳች ስንኳ ያለእርሱ የተፈጠረ ምንም እንደሌለ የተነገረለት አካላዊ ቃል ማለትም ቃለ እግዚአብሔር ወልድ ነው፤
አካላዊ ቃል ከዘመን መቆጠር በፊት በመለኮታዊ ርቀትና ምልአት ከፍጡራን አእምሮ በላይ በሆነ ዕሪና፣ ዋሕድና፣ ቅድምና፣ ኩነትና ህልውና እንደ አብና እንደ መንፈስ ቅዱስ የነበረ ሲሆን በሞቱ የእኛን ዕዳ ኃጢአት ተቀብሎ ከሞተ ኃጢአት ሊያድነን በአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዓመተ ዓለም መጋቢት 29 ቀን መዋች የሆነው ሥጋችንን በማኅፀነ ማርያም ተዋሕዶ ሥጋ ሆነ፤ (ዮሐ. 1፣14)፡፡
ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ሲሆነው ታሕሣሥ 29 ቀን እንደ ትንቢቱ ቃል በዳዊት ከተማ በቤተልሔም ተወለደ፤ የምሥራቹም ‹‹ዛሬ መድኅን ክርስቶስ ተወልዶላችኋል›› ተብሎ በመላእክት አንደበት ተበሠረ፤ (ሉቃ. 2፣10-12፤ ማቴ. 2፣1-11)፡፡
ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋን ተዋሕዶ በተወለደ ጊዜ በቃል ርስትነት ሰው እግዚአብሔር ሆነ፤ በሥጋ ርስትነት አካላዊ ቃል ሰው ሆነ፤ ዕፁብ ድንቅ የሆነ ይህንን ተዋሕዶ የተመለከቱ የሰማይ ሠራዊትም አካለ ሰብእን በተዋሕዶተ ቃል ለአምላካዊ ክብር ላበቃ ለእርሱ ‹‹ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን፤ ሰላምም በምድር ይሁን፤ በጎ ፈቃዱም ለሰው ይሁን›› ብለው በደስታ ዘመሩ (ሉቃ. 2፣13-15)

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!
እግዚአብሔር አምላክ ለሰው ልጅ ያደረገው በጎ ፈቃድ፣ በሰማይም ሆነ በምድር ላሉ ፍጥረታት ለማንም ያልተደረገ ነው፤ (ዕብ. 1፣1-14)፡፡
ምንም እንኳ ፍጥረታትን ሁሉ በቸርነቱ የሚመግብና የሚጠብቅ እርሱ ብቻ መሆኑ ቢታወቅም፣ አካሉን አካል አድርጎ በተዋሕዶ ወደአምላክነት ደረጃ ከፍ ያደረገው፣ በመንበረ መለኮት ያስቀመጠውና የሰማይና የምድር ገዢ ያደረገው ግን ከሰው በቀር ከፍጡር ወገን ሌላ ማንም የለም፤ (መዝ. 8፣4-6፤ ዕብ. 2፣16፤ ኢሳ. 9፣6-7)፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት በተለየ ሁኔታ በስሟ ላይ ‹‹ተዋሕዶ›› የሚለውን ቃል መጠቀሟ የድኅነታችን መሠረት የቃልና የሥጋ ተዋሕዶ መሆኑን ለማሳየት ነው፤
ምክንያቱም ቃል ሥጋን ካልተዋሐደ አይሞትምና፤ ቃል በሥጋ ካልሞተ ደግሞ እኛ ከሞትና ከኃጢአት ዕዳ ነጻ መሆን አንችልምና ነው፤
የአምላክ ሰው ሆኖ መወለድ ለሰው ልጅ ያስገኘለት ክብር እስከዚህ ድረስ መሆኑን መገንዘብና ማወቅ ለሰው ልጅ በጣም አስፈላጊ ነው፤
ክርስቶስ የተዋሐደው ሥጋችን ዛሬ በመለኮት ዙፋን ተቀምጦ ዓለምን ማለትም ሰማያውያኑንና ምድራውያኑን በአጠቃላይ እየገዛ ይገኛል፤ (ዕብ. 2፣5-8)፡፡
ይህ ታላቅና ግሩም ምሥጢር የተከናወነው በሰው ብልሃትና ጥበብ ሳይሆን በእግዚአብሔር ፍቅር ብቻ የተፈጸመ አስደናቂ ጸጋ ነው፤
በዚህ ፍጹም የተዋሕዶ ፍቅር ሰማያውያኑና ምድራውያኑ እውነተኛውን ሰላም ማለትም በጌታችን ልደት የአምላክና የሰው ውሕደት እውን ሆኖ ስላዩ ‹‹ሰላም በምድር ሆነ›› አሉ ፡፡
ሰማያውያኑ ፍጡራን ዛሬም ያለ ማቋረጥ ሰው ለሆነ አምላክ ይህንን የሰላም መዝሙር ይዘምራሉ፤ እኛ ምድራውያኑም የዘወትር መዝሙራችን ‹‹ሰላም በምድር ይሁን›› የሚለው ሊሆን ይገባል፤
ምክንያቱም በሰላም ውስጥ ሃይማኖትን መስበክና ማስፋፋት አለ፤ በሰላም ውስጥ ልማት፣ ዕድገትና ብልፅግና አለ፤ በሰላም ውስጥ መቻቻል፣ መከባበርና  መተማመን አለ፤ በሰላም ውስጥ መደማመጥና መግባባት አለ፡፡
ስለሆነም በልደተ ክርስቶስ ከተዘመረው መዝሙር የሰማነው ዓቢይ መልእክት ‹‹ሰላም በምድር ይሁን›› የሚለው ነውና ከሁሉ በላይ ለእርስ በርስ መፋቀርና ለሰላም መጠበቅ ቅድሚያ መስጠት የዘወትር ግዳጃችን ሊሆን ይገባል፤
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት፤
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደቱን ያደረገው በትሑታኑ መኖሪያ ማለትም በእንስሳቱ በረትና በእረኞቹ ሠፈር እንደነበር ልናስታውስ ይገባል (ሉቃ. 2፡6)
ይህንን ያደረገበት ዓቢይ ምክንያት በእርሱ ዘንድ የተናቀና ዝቅተኛ ነው ተብሎ የሚተው ፍጡር እንደሌለ ለማስተማር ነው (ማቴ. 10፡29-31)
ስለሆነም የእርሱ ደቀ መዛሙርት የሆን እኛም ከልደቱ መልእክት ትምህርትን ወስደን በዚህ ቀን በጤና፣ በዕውቀት፣ በሀብትና በልዩ ልዩ ምክንያት አካላዊ፣ ሥነ ልቡናዊና ቁሳዊ ድህነት ከተጫናቸው ወገኖች ጋር አብረን በመዋል፣ አብረን በመመገብና እነርሱን ዘመድ በማድረግ በዓሉን ልናከብር ይገባል፤ (ማቴ. 25፡40)፡፡

በመጨረሻም፤
ልደተ ክርስቶስ መለያየትንና ጥላቻን ያስወገደ፤ በምትኩ እግዚአብሔርንና ሰውን በማዋሐድ ለሰው ልጅ አዲስ የድኅነት ምዕራፍን የከፈተ እንደሆነ ሁሉ፣ እኛ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያትም ድህነትን በአጠቃላይ ለመቀነስ የጀመርነው አዲስ የልማትና የዕድገት መርሐ ግብር ከግብ ለማድረስ አሁንም ሌት ተቀን ጠንክረን በመሥራት ሀገራችንን በልማት እንድናሳድግ አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን ፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝባችንን ይባርክ፤ ይቀድስ፡፡
አሜን!

አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ታሕሣሥ 29 ቀን 2007 ዓ.ም.
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

 
ለቅዱሳን ፓትርያርኮችና ለብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጸሎተ ፍትሐት ተደረገላቸው

i03

ከአጸደ ሥጋ ዓለም በሞት ተለይተው በአጸደ ነፍስ የሚገኙ ቅዱሳን ፓትርያኮችና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ ጥቅምት 9 ቀን 2007 ዓ.ም በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ጸሎተ ፍትሐት ተደረገላቸው፡፡  ጸሎተ ፍትሐቱ በተለይ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ፣ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ፣ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖትና ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ፣እንዲሁም ለብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳት ነው፡፡
 ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በዕለቱ በሰጡት ቃለ ምዕዳን “አባቶቻችን ርእሳነ ሊቃነ ጳጳሳት በሕይወተ ሥጋ ሳሉ ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበሉትን አደራ ጠብቀው በሚችሉት አቅም ሊሠሩት የሚገባውን ሁሉ ሠርተው አልፈዋል፡፡ በተጨማሪም ቤተ ክርስቲያንን ጠብቀውና ሃይማኖትን አጽንተው በማቆየት ለእኛ አስተላልፈዋል” ብለዋል፡፡
ቅዱስነታቸው አያይዘውም “እናትና አባትህን አክብር የሚለውን የጌታን ትእዛዝ ለመፈጸም በዚህ ቦታ ተገኝተናል በመንፈስ ወልደውና በምግባር አሳድገው ለዚህ ስላበቁን እነሱን ማክበርና ማስታወስ ግዴታችን ነው፡፡ ስለሆነም ይህ መታሰቢያ በዓል በየዓመቱ እንዲከበር በቅዱስ ሲኖዶስ መወሰኑ የሚመሰገን ነው፡፡” በማለት ቀደምት የቤተክርስቲያን አበውን መዘከር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡


የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የወላይታ ኮንታና ዳውሮ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ “ሰው በዚህ ዓለም ይሞታል፤ የማይሞተው ግን የሠራው ሥራ ነው፤ ለሰው ሐውልቱ ሥራው ነው ስለሆነም ዛሬ የዘከርናቸው እንደነ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ፣ ቴዎፍሎስ፣ ተክለ ሃይማኖትና ጳውሎስ ስማቸው ሕያው ነው፡፡ ብለዋል፡፡
በዚሁ እለት የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የመታሰቢያ ሐውልት ተመርቋል፡፡ የመታሰቢያ ሐውልቱ የተሠራው በቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያና ትዕዛዝ ሲሆን፤ ወጭውን ደግሞ ጠቅላይ ቤተ ክህነት መሸፈኑን የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጁና የወላይታ ኮንታና ዳውሮ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ አስታውቀዋል፡፡
ብፁዕ ሥራ አስኪያጁ ስለ ሐውልቱ መሠራት ሲገልጹ “የቅዱስ አባታችን የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ሐውልት በዚህ ቦታ የተተከለው ለመታሰቢያነት እንጂ ሐውልታቸው በሕይወተ ሥጋ ሳሉ በመላው ኢትዮጵያ የሠሩት ሥራ ነው፡፡
በዚህም ዘለዓለም ሲታሰብ ይኖራል፡፡ ሰው በታላቅነቱና በሠራው ሥራ ሲታወስ ይኖራል፤ እኒህ ታላቅ አባትም በዚህ ስፍራ የቆመው ሐውልት ለመታሰቢያነት እንጂ ሐውልታቸው በሔዱበት ቦታ ሁሉ የሠሩት ሥራ ነው፡፡ ” ብለዋል፡፡


በዕለቱ የቅዱሳን ፓትርያርኮችና ብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳት  ጸሎተ ፍትሐትና የመታሰቢያ ሐውልት ምርቃት መርሐ ግብር ቅዱስ ፓትርያርኩ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስን ጨምሮ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የ33ኛው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ተሳታፊዎች የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና በርካታ ምእመናን ተገኝተዋል፡፡

 
የካቴድረሉ ዋና አስተዳዳሪ ሆነው የተሾሙት ክቡር ሊቀ ስልጣናት አባ ገ/ሥላሴ በላይ ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው

0022

በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት መልካም ፈቃድ ከነሐሴ 1 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም. ጀምሮ  የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ዋና አስተዳዳሪ ሆነው የተሾሙት ክቡር ሊቀ ስልጣናት አባ ገ/ሥላሴ በላይ ሲሆኑ ሐሙስ ነሐሴ 1 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም. የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሰበካ ጉባዔ አባላት፣መላው ማህበረ ካህናት፣ መዘምራን፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችና የአጥቢየው ምእመናን  ደማቅ አቀባበል አድርጐላቸዋል፡፡

ክቡር ሊቀ ስልጣናት አባ ገ/ሥላሴ በላይ በካቴድራሉ ሲሾሙ አሁን ለ2ኛ ጊዜ ሲሆን ቀደም ሲል ከ2004 እስከ 2005 ዓ.ም ካቴድረሉን ባስተዳደሩበት ጊዜ ብዙ ሥራ እና መልካም አስተዳደር ከማስፈናቸውም በላይ ለካቴድራሉ መንፈሳዊ እና ለሁለንተናዊ አገለግሎት የሚሆን ብዙ ገንዘብና ጥሬ እቃ ካሰባሰቡ በኋላ በደብረ ገነት መካኒሳ ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል ማህበረ ካህናትና ማህበረ ምእመናን ጥያቄ አማካኝነት ለ1 ዓመት ያህል ወደ መካኒሳ ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል ሄደው ዘርፈ ብዙ ልማት ካለሙ  በኋላ ልክ በ1 አመታቸው በካቴድራሉ ማህበረ ካህናት እና ልይ ልዩ ሠራተኞች ጥያቄና በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት መልካም ለ2ኛ ጊዜ የካቴድራሉ ዋና አስተዳዳሪ ሆነው ተሹመው መጥተዋል፡፡ክቡር ሊቀ ስልጣናት አባ ገ/ሥላሴ በላይ ወደ ካቴድራሉ በድጋሚ እንዲመጡ የተመረጡበት መክንያት መንፈሳዊና የልማት አባት በመሆናቸው ሲሆን ከአሁን በፊት የሠሯቸው ሥራዎች ትላልቅ ማረጋገጫዎች ናቸው፡፡


በክብረ በዓሉ ላይ ብፁዕ አቡነ አረጋዊ የካቴድራሉ የበላይ ጠባቂና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ፤የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች  ፤የደብረ ገነት መካኒሳ ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል ካህናት፤የካቴድራሉ ማህበረ ካህናትና ልይ ልዩ ሠራተኞች በክብረ በዓሉ ላይ ተገኝተዋል፡፡ በዓሉን አስመልክቶም የተለያዩ ቅኔዎችና ዝማሬዎች በካቴድራሉ ሊቃውነት  አማካኝነት ቀርቧል፡፡
በስተመጨረሻ የተደረገላቸውን አቀባበል በማስመልከት ንግግር ያደረጉት ክቡር ሊቀስልጣናት አባ ገ/ሥላሴ በላይ ሲሆኑ የተደረገላቸውን አቀባበል ካመሰገኑ በኋላ ካቴድራሉ ዓለም አቀፋዊ እንደመሆኑ መጠን በልማትና በመልካም አስተዳደር ወደተሻለ ደረጃ ላይ እንዲደርስ የሁሉም ሠራተኛ እና ምእመናን አስተዋጽኦ ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ከዚሁ ጋር አያይዘውም ዘመኑ በሚፈቅደው አስተሳሰብና አሰራር ሰዎች መሥራት ይኖርብናል ብለዋል፡፡ ሥርዓተ ቅዳሴው በክቡር ሊቀ ስልጣናት አባ ገ/ሥላሴ በላይ መሪነት ከተከናወነ በኋላ የበዓሉ ፍፃሜ ሆኗል፡፡
መልካም የሥራ ዘመን እንዲሆንላቸውም ሁሉም የካቴድራሉ ሠራተኞች ተመኝተውላቸዋል፡፡

 
ዓመታዊው የዓጋዕዝተ ዓለም ሥላሴ ክብረ በዓል በድምቀት ተከበረ

g0027

በየዓመቱ ሐምሌ 7 ቀን በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የሚከበረው ዓመታዊው የሥላሴ በዓል በዚህ ዓመትም በመንበረ ጸባዖት ቅድሰት ሥላሴ ካቴድራል ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኩሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ ብፁአን ሊቃነ ጳጳሳት እንዲሁም በብዙ ሽህ የሚቆጠሩ ምዕመናን በተገኙበት እጅግ በጣም ደማቅ በሆነ ሁኔታ በዓሉ ተከብሮ ውልዋል፡፡
በዚሁ ዕለት አጋዕዝተ ዓለም ሥላሴ በአብርሃም ቤት ተገኝተው ቤቱን የባረኩበት፣ የአንድነታቸውንና ሶስትነታቸው ሚስጢር የተገለፀበት ታላቅ በዓል ነው። በዓሉ መከበር የጀመረው ከዋዜማው ከሐምሌ6 ጀምሮ ሲሆን የካቴድራሉ ካህናትና መዘምራን ከዋዜማው ከቀኑ 3 ሰዓት ጀምሮ ለ30 ሰዓታት ያህል ሌሊትና ቀኑን ሙሉ ያለ ማቋረጥ ስብሃተ እግዚአብሔር ሲያቀርቡ ውለው አድረዋል፡፡
ይህመንፈሳዊ አገልግሎት ማለትም ስርዓተማህሌተ፣ ስርዓተቅዳሴ እንዲሁም ሰዓታትና ሰርክ ፀሎት በአጠቃለይ የስርዓተ አምልኮ አፈፃፀም በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ልዩ በመሆኑ የእምነቱ ተከታዮች ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም እጀግ በጣም የሚያስደንቅ በዓል ነው፡፡በክብረ በዓሉ ላይ የተገኙት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኩሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ሥርአተ ቅዳሴውን የመሩት ሲሆን በካቴድራሉ አውደ ምህረት ላይ ተገኝተውም  በአሉን ለማክበረ ከተለያየ ቦታ ለመጡ ምዕመናን በዓሉን አስመልክተው ሰፋ ያለ ትምህርተ ወንጌል ሰጥተዋል፡፡

 
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የ2006 ዓ.ም.የትንሣኤ በዓልን አስመልክቶው ቃለ ምዕዳን አስተላለፉ

0908

ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት
በእንተ ትንሣኤሁ ለእግዚእነ ወአምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
•    በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣
•    ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምኖሩ፣
•    የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፣
•    በሕመም ምክንያት በየሆስፒታሉ ያላችሁ፣
•    እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት በሙሉ፤
እርሱ ሕያው ሆኖ ሕያዋን መሆናችንን በትንሣኤው ላበሠረን ለጌታችን  ለአምላካችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ትንሣኤ እንኳን በሰላም አደረሳችሁ!!
‹‹ወርኢናሃ ለሕይወት፤ ወተዐውቀት ለነ፤
ሕይወትን አየናት፣አወቅናትም›› (1ዮሐ1÷2)
የሕይወት መገኛና ምንጭ አምላካችን እግዚአብሔር ነው፣ ከእግዚአብሔር የተገኘው ሕይወት የሰው ልጅ የዕውቀት ብርሃን ነው፤ አምላካዊ ሕይወት ካለው ሰው የሚፈልቅ ብርሃናዊ ዕውቀት ጽልመታዊውን ዓለም በብሩህነቱ ያሸንፋል እንጂ በጽልመታዊ ዓለም አይሸነፍም፡፡ (ዮሐ.1÷4-5)
    የሰው ልጅ ሕያው አምላክ በመልኩና በአምሳሉ የፈጠረው ፍጡር በመሆኑ  ሕያውና ክቡር፣ ዘላለማዊና ብርሃናዊ፣ የማሰብ፣ የማመዛዘን፣ የመምረጥና፣ የመወሰን ነጻነት ያለውና ከሌሎች ፍጥረታት ሁሉ የላቀ አእምሮ ያለው ልዑል ፍጡር ነው፤
    ሰው ከእግዚአብሔር በተሰጠው ነጻነትና አእምሮ መሠረት ነጻነቱን ተጠቅሞ የመረጠውን የማድረግ ነጻነት ያለው ፍጡር ቢሆንም በነጻ ዕውቀቱና ምርጫው ለሚፈጽመው ሁሉ እርሱ  ራሱ ኃላፊነቱን ይወስዳል፤
ይህም ማለት በምርጫው መሠረት የሚሠራው ሥራ ሁሉ በእውነተኛው ዳኛ በእግዚአብሔር ፊት መልካም ሆኖ ከተገኘ ምስጋናን፣ መልካም ሆኖ ካልተገኘ ግን ተጠያቂነትንና ፍርድን ያስከትልበታል ማለት ነው፡፡
ከዚህ አንጻር የመጀመሪያ ሰው የሆነው አዳም ማድረግ ያለበትንና ማድረግ የሌለበትን ተለይቶ ከእግዚአብሒር ቢነገረውም የተነገረውን ሕግ ወደጎን ገሸሽ በማድረግ የራሱን ነጻ ምርጫ ተጠቅሞ ‹‹አትብላ›› የተባለውን በላ፤
በመሆኑም ይህ ድርጊት በእግዚአብሔር ዘንድ እጅግ ታላቅ ስሕተትና ድፍረት  ነበረና ተጠያቂነትን አስከተለ፣ በመጨረሻም ሕይወትን የሚያሳጣ የሞት ፍርድንና ቅጣትን በራሱና በልጆቹ ሁሉ ላይ አመጣ፡፡
ፍርዱ ሥራ ላይ ከዋለበት ቀን ጀምሮ ሰው ሕይወቱን አጣ ማለትም ከእግዚአብሔር አንድነት ተለየ፤ ሞትና ሲኦልም ሰውን ከእግዚአብሔር ለይተውና የራሳቸው ተገዥ አድርገው እስከ ስቅለተ ክርስቶስ ድረስ በቁጥጥራቸው ሥር አዋሉት፡፡
ሆኖም እግዚአብሔር በባህርዩ መሐሪና ፈራጅ እንደመሆኑ መጠን ለፈራጅነቱና ለመሐሪነቱ የሚስማማ መንገድ አመቻችቶ መሐሪነቱንና ፈራጅነቱን በፈጸመበት በክርስቶስ ሞት ቤዛነት የሰው ልጅን ታረቀው፤ ያጣውንም ሕይወት መለሰለት፤ በምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አማካኝነትም እንደገና ሕይወቱን እንዲያገኝ አደረገ (ዮሐ. 6÷56-58፤ ማር 16÷16)
    ይህን አስመልክቶ ቅዱስ ጳውሎስ ሲናገር‹‹በመጀመሪያው ሰው (አዳም) ሞት መጣ፣ በሁለተኛው ሰው (ክርስቶስ) ግን ትንሣኤ ሙታን ሆነ፤ሁሉም በአዳም እንደሚሞቱ እንደዚሁ ሁሉም በክርስቶስ  ሕያዋን ይሆናሉ›› ብሏል፤ (1ቆሮ 15÷21-22፤ሮሜ 5-12-19)
ከዚህ የምንረዳው ዓቢይ ቁም ነገር በአዳም አለመታዘዝ ምክንያት ያጣናት ሕይወት፣ በክርስቶስ መታዘዝ ያገኘናት መሆናችንን ነው፤ ጌታችንም ‹‹ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ሕያው የሆነም፣ የሚያምንብኝም፣ ሁሉ ለዘላለም አይሞትም፤እኔም በመጨረሻይቱ ቀን አስነሣዋለሁ›› ብሎ ትንሣኤና ሕይወት መሆኑን እንደነገረን የሰው ልጅን ለዘላለማዊ ሕይወት እንደገና አበቃው (ዮሐ. 6÷54፤ 11÷25-26)
የዚህም እውነታ በትንሣኤው አበሰረን፣ የእርሱ ትንሣኤ የትንሣኤያችን ዋዜማ ነውና የቀደመችው ሕይወት እንደተመለሰችልን በትንሣኤው አየናት፤ አወቅናትም፤(ኤፌ.4÷5-7)
        የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ ምእመናንና ምእመናት
     የክርስቶስ ትንሣኤ ለሰው ልጅ የዘላለማዊ ሕይወት ማረጋገጫ ነው፤ለበርካታ ዘመናት በተስፋ ይጠበቅ የነበረው የክርስቶስ ነገረ አድኅኖ እና ነገረ ትንሣኤ በጊዜው ጊዜ እውን እንደሆነ ሁሉ፣ እንደዚያው በተስፋና በእምነት እየተጠባበቅነው ያለ የሰው ልጅ ሕይወታዊ ትንሣኤ ጊዜው ሲደርስ በክርስቶስ ዳግም ምጽአት እውን ይሆናል፤(1ቆሮ 15÷20-23፤1ተሰ 4÷13-18)
 ይሁን እንጂ ዛሬም ሕይወትን በሚሰጥ በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ያለን ስለሆን የሕይወትን ጣዕም አሁንም ማጣጣም እንችላለን፤ ሕይወት ጣዕም የሚኖረው በፍቅር ሲታጀብ ነው፣ ፍጹም ፍቅር የዘላለማዊ ሕይወት ኃይል ነው፤ ፍቅር ፍጹም የሚሆነው ሦስቱን አቅጣጫዎች ማእከል አድርጎ ሲገኝ ነው፤
 ይኸውም ወደ ላይ እግዚአብሔርን በፍጹም ፍቅር መከተል ስንችል፣ ወደጎን በአርአያ እግዚአብሔር የተፈጠረውን የሰው ልጅ በአጠቃላይ መውደድ ስንችል፣ ወደ ታች ደግሞ የምንኖርባትን ምድርና በውስጧ ያሉ ፍጥረታትን ስንንከባከብ ነው፣ ይህን ካደረግን ፍጹም ፍቅር ከእኛ  አለ ማለት እንችላለን፤ እግዚአብሔር ይህንን ዓይነት ፍቅር እንዲኖረን በሃይማኖት አስተምሮናል፡፡
    በመሆኑም እኛ ክርስቲያኖች ለእግዚአብሔር ያለንን ፍቅር ለመግለጽ በመዋዕለ ጾሙ በአምልኮ፣ በጾም፣ በጸሎት፣ በምጽዋትና በስግደት ስንገልጽ እንደቆየን ሁሉ፣ በፋሲካው በዓላችን እግዚአብሔር የሰጠንን በረከት ከተቸገሩ ወንድሞቻችንና እኅቶቻችን ጋር በመካፈል ለወገኖቻችን ያለንን ፍቅር ልንገልጽ ይገባናል፤
በዚህ ዕለት በዓሉን ስናከብር የተራቡትን በማብላት፣ የተጠሙትን በማጠጣት፣ የታረዙትን በማልበስ፣ ጧሪ የሌላቸው አረጋውያን፣ አሳዳጊ የሌላቸው ሕጻናት፣ በልዩ ልዩ ምክንያት የአካልና የአእምሮ ጉዳት ደርሶባቸው የበይ ተመልካች የሆኑ ወገኖች ሁሉ ከእኛ ጋር በማዕዳችን ተሳታፊ ሆነው በዓሉን በደስታና በምስጋና እንዲያከብሩ ማድረግ ክርስቲያናዊ ግዴታችን ነው፡፡
            የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ ምእመናንና ምእመናት
የትንሣኤ መሠረታዊ ትርጉም ከሞት በኋላ በሕይወት መኖርና መመላለስ ነው፤ ስለሆነም የትንሣኤን በዓል ስናከብር ባለፉት ዘመናት በድህነትና በኋላ ቀርነት ከሞት አፋፍ ደርሳ የነበረችውን ሀገራችን በልማትና በዕድገት ትንሣኤዋን ለማረጋገጥ ቃል በመግባት በዓሉን ማክበር ሀገራዊ ብቻ ሳይሆን ሃይማኖታዊ ግዴታ መሆኑን መገንዘብ አለብን፤
 ምክንያቱም ጠንክረን በመሥራት ምድራችንን እንድናለማና እንድንከባከብ ከሁሉ በፊት ያዘዘ እግዚአብሔር ነውና፤ በተለይም የልማታችን የጀርባ አጥንት ሆኖ እንደ ሚያገለግል ታላቅ ተስፋ የተጣለበት ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በተያዘው ፍጥነት ሥራው ተሠርቶና ተጠናቆ የዕድገታችን ተሸካሚ ምሶሶ ሆኖ ማየት እንድንችል ሁሉም ኢትዮጵያዊ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ቤተ ክርስቲያናችን ጥሪዋን ታስተላልፋለች፤
    የሀገራችን የልማትና የዕድገት መርሐ ግብሮች ዘርፈ ብዙ እንደመሆናቸው መጠን ገበሬው በየአካባቢው እያከናወነው የሚገኝ አፈርን የመገደብና አካባቢን በአረንጓዴ ልማት የማስዋብ ሥራ ያለመቋረጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በማድረግ ረገድ ቤተ ክርስቲያችን በግባር ቀደም ተሰልፋ እንደምትሠራ በዚህ አጋጣሚ ለማረጋገጥ እንወዳለን፡፡
    በአሁኑ ጊዜ በሥራ ላይ ያሉም ሆኑ ወደፊት ሊሠሩ በእቅድ የተያዙ የሀገራችን የልማትና የእድገት ሥራዎች በሕዝቡ የተባበረ ድጋፍ ሲከናወኑ የሀገራችን ብልጽግና እውን እንደሚሆን የሁላችንም እምነት ነው
ስለሆነም ለዚህ ስኬት የኢትዮጵያውን ሁሉ ጽናት፣ አንድነት፣ ስምምነትና ፍቅር፣ ሰላምና ተቻችሎ መኖር የማይተካ ሚና እንዳላቸው ለአፍታ እንኳ መዘንጋት የለብንም፤
          የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ ምእመናንና ምእመናት
ልማታችን በተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ ብቻ ሳይሆን የተቀደሰውና የተከበረው ባህላችንና ሰብኣዊ ሥነ ምግባራችንን ጠብቆ በማስጠበቅ ጭምርም መሆን ይገባዋል
ኢትዮጵያ ሀገራችን ከጥንት ጀምሮ በቅዱሳት መጻሕፍት ሀገረ እግዚአብሔር ነች ተብሎ በተደጋጋሚ የተነገረላት ያለምክንያት አልነበረም
ኢትዮጵያውያን አባቶቻችን በማናቸውም ጊዜ ከነውረ ኃጢአትና ከርኩሰት ሁሉ ርቀው፣ ሕገ ተፈጥሮንና ሕገ እግዚአብሔርን ጠብቀው፣ እግዚአሔር የሚለውን ብቻ አዳምጠውና አክብረው የሚኖሩ ቅዱሳን በመሆናቸው እንጂ
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ምድር ሊፈጸም ቀርቶ ሊወራ የማይገባውን ሰዶምንና ገሞራን በእሳት ያጋየ ግብረ ኃጢአት በኢትዮጵያ ምድር መሰማቱ እግዚአብሔር ለኢትዮጵያውያን የሰጠውን የቅድስና ክብር የሚያሳጣ ከመሆኑም ሌላ በሀገራችን ላይ ልማትና ዕድገት ሳይሆን መቅሰፍትና ውድቀት እንዳያስከትልብን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ይህንን የሰዶም ግብረ ኃጢአት በጽናት መመከት አለበት፤
ተፈጥሮን ለማልማት እየተረባረብን እንደሆነ ሁሉ ከዚህ ባልተናነሰ ሁኔታ የሰዶም ግብረ ኃጢአትን በመከላከል በቅዱስ ባህልና ሥነ ምግባር እጅግ የበለፀገና የለማ ትውልድ ማፍራት የልማታችን አካል ማድረግ አለብን፤
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ይህንን ግብረ ኃጢአት እስከ መጨረሻው ድረስ አምርራ የምትዋጋው መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ለመላው ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ማረጋገጥ እንፈልጋለን፤  ስለሆነም ሕዝባችን ለሰላምና ለአንድነት፣ ለእኩልነትና ለልማት፣ ለቅዱስ ባህልና ሥነ ምግባር ቅድሚያ ሰጥቶ በሁሉም አቅጣጫ ልማቱን እንዲያፋጥን፣ ሃይማኖቱንም እንዲጠብቅ መልክታችንን እናስተላልፋለን፡፡
መልካም የትንሣኤ በዓል ያድርግልን!!
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝባችንን ይባርክ  ይቀድስ አሜን !!

አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖ
ሚያዝያ 12 ቀን 2006 ዓ.ም
አዲስ አበባ

 
ዝርዝር ፅሁፍ...
<< ጀምር < ወደኋላ 1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 ወደፊት > መጨረሻ >>

ገጽ 7 ከ 20

የቤተክርስቲያን አድራሻ

የካቴድራሉ ሰበካ ጉባዔ ጽ/ቤት
ስልክ ፤ 011-1-23-35-18 / 011-1-23-35-15
አዲስ አበባ
ኢትዮጵያ
church@trinity.eotc.org.et
www.trinity.eotc.org.et

ግጻዌ

ማስታወቂያ

ለመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እድሳት የበኩልዎን አስታዋጽዖ ያድርጉ!

መርዳት የምትፈልጉ ምዕመናን ሁሉ የሚከተለውን አድራሻ መጠቀም ትችላላችሁ፡፡

አራት ኪሎ ቅርንጫፍ, ቁጥር= 0171859072600/2637 (መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እድሳት )

ብላች መላክ ትችላላችሁ፡፡